በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለዳሎቻ እና አዲሎ ዙርያ ወረዳዎች የመረጃ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችሉ የዲጂታል ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ ነሀሴ 2018 ዓ.ም (ሆሳዕና)

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በወረዳ ደረጃ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የመረጃ ስርዓትን ዘመናዊ ለማድረግ እና የማስፈጸም አቅምን ለማጠናከር ያለመ የዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች እና የፕሪንተር ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ። ይህ የቁሳቁስ ድጋፍ በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው “የምዕራፍ ሁለት ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አመራር ማጠናከሪያ ፕሮጀክት” (EU-DRM Phase II) አካል ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ ለታቀፉት ለዳሎቻ እና ለአዲሎ ዙርያ ወረዳዎች የተበረከተ ነው። በቁሳቁስ ርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የአደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዋንጎሮ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በክልሉ የአደጋ ስጋት መረጃዎችን በጥራት የመሰብሰብ፣ የማደራጀት እና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማሳደግ የመረጃ ስርዓቱን የማዘመን ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል። አክለውም የዛሬው ድጋፍ በወረዳ ደረጃ ያለውን የመረጃ ልውውጥ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራን የበለጠ ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። በእለቱ የተገኙት የኮሚሽኑ አማካሪ አቶ ይርጋ ሀንዲሶ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ሕብረት ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አመራር ማጠናከሪያ ፕሮጀክት በክልሉ የአደጋ ስጋትን በመቀነስና የአካባቢውን ህብረተሰብ የማቋቋም አቅም በመገንባት ረገድ እያበረከተ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አድንቀዋል። በተደረገው ድጋፍ መሰረት የተረከቧቸው ዘመናዊ የዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች እና ኤችፒ (HP LaserJet) ፕሪንተሮች በወረዳዎቹ የሚከናወኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር መረጃዎችን በአግባቡ ለመያዝ፣ ለመተንተን እና ለሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ለማድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል። ኮሚሽኑ በቀጣይም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋት ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስርዓትን የበለጠ ለማጠናከር ከደጋፊ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።


One Reply to “በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለዳሎቻ እና አዲሎ ዙርያ ወረዳዎች የመረጃ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችሉ የዲጂታል ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ ነሀሴ 2018 ዓ.ም (ሆሳዕና)”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *